በ2015 አጋፔሜድ በሆለታ ከተማ ያካሄደው አገልግሎት

b1

 

በእህት አደይ አበበ

ሚኒሶታ በምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማለትም በፓስተር እንድርያስ ሐዋዝ እና በወንጌላዊ ዮሐንስ በለጠ ልብ ውስጥ እግዚአብሔር ባስቀመጠው ራዕይ መሰረት የተጀመረው አጋፔሜድ (AgapeMED) የተሰኘው አገልግሎት በተለያየ የህክምና ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የቤተክርሰቲያኒቱን አባላት ያሳተፈ የአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ይህ የአገልግሎት ዘርፍ በሚኒሶታ ከሚያካሂደው አገልግሎት ባሻገር ከወንጌል ስርጭት በተጓዳኝነት በአመት አንድ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የጀማው ስብከት ከሚካሄድባቸው ሁለት ከተሞች መካከል በአንዱ ከተማ ላይ አገልገሎቱን እንዲሰጥ ታቅዷል፡፡

በዚህም መሰረት፤ እ.አ.አ ከጃንዋሪ 27 እስከ ፌብርዋሪ 3,2015 ድረስ በሆለታ ከተማ በመገኘት ከኢትዮጵያ ክርስቲያን ሜዲካል ዶክተሮችና የጥርስ ሀኪሞች ህብረት (Christian Medical Doctors and Dentist Fellowship) CMDDF ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን የጤና አገልግሎት አካሂዶ ተመልሷል፡፡ ከአሜሪካን ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በተለያዩ ቀናት በልዩልዩ አገልግሎት የተሳተፉት ወገኖች ቁጥር 18 ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ከሚገኘው ክርስቲያን ዶክተሮችና የጥርስ ሀኪሞች ህብረት ተውጣጥተው በተለያዩ ቀናት ወደስፍራው በመምጣት ያገለገሉ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የምክር አገልግሎት ሰጪ ወገኖች ቁጥር ደግሞ ወደ 45 ይጠጋል፡፡

ቡድኑ በአብዛኛው የተጠቀመባቸውን መሳሪያዎች ሚኒሶታ ከሚገኘው ማተርስ ከተሰኘ እርዳታ ሰጪ ድርጅት ያገኘ ሲሆን፤ ሌሎች በርካታ ግለሰቦችም ያበረከቱለትን መሳሪያዎች ይዞ በመሔድ ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የክርስቲያን ሀኪሞች ህብረትም አስቀድሞ አስፈላጊ መድሐኒቶችን በመግዛትና አንዳንድ ጠቃሚ መሳሪያዎችን ስፍራው ድረስ በማምጣት ስራው በተቃና ሁኔታ እንዲከናወን ከፍተኛ ትብብር አድርጓል፡፡ ሆለታ ከተማ ከአዲስ አበባ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ሲሆን እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በሁለት ሺህ አመተ ምህረት የህዝብ ቆጠራ መሰረት 40,077 ሰወች ይኖሩባታል ተብሎ ይገመታል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን አማርኛ፤ጉራጌኛ፤ትግሪኛ፤ወላይትኛ እና የሀድያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይገኙበታል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው በንግድ ስራ፤በመንግስት ስራና በእርሻ ልማት ነው፡፡ ጤናን በተመለከተ በከተማው ሁለት የጤና ጣቢያና 12 የግል ክሊኒኮች ይገኙበታል፡፡

ይሁን እንጂ አንድም ሆስፒታል የለም፡፡ ላቅ ያለ ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሲኖሩ ወደ አዲስ አበባ ሄደው ህክምና እንዲከታተሉ ይደረጋል፡፡ የከተማውን ህዝብ ያጠቃሉ ተብሎ የሚገመቱ የጤና ችግሮች፡- • የሳንባ ነቀርሳና ኒሞንያ • የቆዳ በሽታ • የሆድ እቃ ችግር • ታይፎይድና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን • የጨጓራ በሽታ • የአይን በሽታ • ኤች.አይ.ቪ • የጀርባ በሽታ • የስኳር በሽታና የደም ግፊት ናቸው፡፡ የከተማውን ነዋሪ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ይኸው የህክምና ቡድን እና ከኢትዮጵያ ክርስቲያን ሜዲካል ዶክተሮችና የጥርስ ሀኪሞች ህብረት በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለመሰማራት የመጡት ባለሙያዎች በጋራ በሆለታ ከተማ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ በመገኘት የህክምና አገልግሎታቸውን በፍቅርና በትህትና ለህዝቡ አበርክተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በወቅቱ በተደረገው የህክምና አገልግሎት በአጠቃላይ 2,866 ሰወች የተለያየ የህክምና አገልግሎት አግኝተዋል፤ ከነዚህም መካከል፡- • 523 ህፃናት ህክምና ያገኙ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም • 1,064 ሰዎች የውስጥ ደዌ ህክምና • 114 ሰዎች የቆዳ ህክምና • 150 ሰዎች የአንገት በላይ ህክምና • 72 ሰዎች ቀላል የቀዶ ጥገና አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከባድ የቀዶ ጥገና ሊደረግላቸው ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች አዲስ አበባ ለሚገኝ ሆስፒታል ሪፈራል ተፅፎ ተሰጥቷቸዋል፡፡ • የጥርስ ህክምናን በተመለከተም 213 የተበላሸ ጥርስ ያላቸው ሰዎች ጥርሳቸው የወለቀላቸው ሲሆን፤ 68 ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከጥርስ ጋር የተያያዘ የጤና አጠባበቅ ምክር ተሰጥቷል፡፡ • 652 ሰዎች የአይን ህክምና ሲያገኙ፤ ከነዚህም መካከል በርካታ ሰዎች እንደደረሰባቸው የአይን ችግር ደረ,ጃ መነፅር እንዲያገኙ ሲደረግ፤ ሌሎች ደግሞ የመድሀኒት፤የምክርና የሪፈራል አገልግሎት ተሰጥቷል፡፡ • የተለያየ የውስጥ ህክምና ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል ከተለያየ ምርመራ ክፍል የተላኩ 443 የሚሆኑ በሽተኞች በጤና ጣቢያው በሚገኘው ላቦራቶሪ የተለያየ ምርመራ ስራ ተደርጎላቸዋል፡፡ ሙያነክ ከሆኑት አገልግሎቶቸ በተጓዳኝነትም የተለያየ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ምርመራቸውን ጨርሰው ወደቤታቸው ከመሄዳቸው በፊት በተለያዩ አማካሪዎች አማካኝነት የደህንነትን ወንጌል ተመስክሮላቸዋል፡፡

የዚህ አገልግሎት ዋና አላማ በሐዋርያት ስራ 4፡12 ላይ እንደምናገኘው "መዳን በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና" በሚለው መሰረት ሰዎችን በየምስራቹ ወንጌል መድረስ ነው፡፡ ክርስቶሰ ኢየሱስ ለችግራቸው መፍትሔ ፈልገው ወደ እሱ የመጡትን ሰዎች ሁሉ ለችግራቸው መፍትሄ ከሰጠ በኋላ የህይወትን ቃል ይመግባቸው እንደነበር በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ በተለያየ ስፍራ ተጠቅሷል በዚህም መሰረት ከሰሙት ቃል የተነሳ ብዙዎች በእርሱ ያምኑ እንደነበር ሁሉ፤ በነዚህም ቀናቶች ውስጥ የጤና ምርመራ ለማግኘት የመጡት ሰዎች ምርመራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የወንጌል ምስክርነት ወደሚሰጥበት ክፍል በመላክ የክርስቶስን አዳኝነት የሚያበስረውን ቅዱስ ወንጌል እንዲሰሙ ተደርጓል፡፡ የሰሙትንም ቃል ልባቸውን ከፍተው በእምነት የተቀበሉ 328 ሰዎች በፈቃዳቸው ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ አድርገው ተቀብለዋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ፤ የተፈወሱ እና ከአጋንንት እስራት ነፃ የወጡም ጥቂት ሰዎችይገኙበታል፡፡ ቀደም ሲል ጌታን የሚያውቁ ክርስቲያኖችም የመፅናናት የፀሎት አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ ለመዛል የቀረቡት እና ጌታን ከመከተል የተመለሱት ደግሞ በንስሀ እንደገና ህይወታቸውን እንዲያዱሱ በፀሎት ታግዘዋል፡፡ በአገልግሎቱ ማብቂያም በወረዳው ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ተወካዮች ጌታን የተቀበሉትን ሰዎችና መበረታታት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ስም ዝርዝርና ስልክ ቁጥር በመስጠት ቀጣይ ክትትል እንዲደረግላቸው ሀላፊነት ተሰጥቷል፡፡ በሚሽኑ ማብቂያ ቀንም ከሚኒሶታ የተላከው የአጋፔሜድ ቡድን ቀኑን ሙሉ የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ተጠቂ የሆኑ ህፃናትና ወላጅ አልባ የሆኑ በርካታ ህፃናትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ የተለያ የመዝናኛ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አብሮ ውሏል፡፡ ህፃናቱን ይዘው ለመጡ ወላጆችና አሳዳጊዎችም የተለያየ ጤና ነክ ትምህርቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡

ይኸው ቡድን በቀጣዩ አመትም ማለትም እ.አ.አ በ2016 ተመሳሳይ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ክርስቲያን የሜዲካል ዶክተሮችና የጥርስ ሀኪሞች ጋር በመተባበር በሻሸመኔ ከተማ በመልካ ኦዳ ሆስፒታል ለመስጠት ያቀደ ሲሆን፤ በዚህ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ የምትፈልጉ ወገኖች ሁሉ የአጋፔሜድን ድረገፅ (www.agapemed.org) በመጎብኘት አስፈላጊውን መረጃ በማግኘት መመዝገብ እንደምትችሉ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡ ስራው እጅግ በጣም ሰፊ በመሆኑ እግዚአብሔር ልቡን ለዚህ የተቀደሰ ስራ ያነሳሳው በጎ ፈቃድኛ ሁሉ መሳተፍ እንደሚችል በዚህ አጋጣሚ ሳናሳስብ አናልፍም፡፡ የህክምና ቡድኑን በሞገስ አውጥቶ፤ መከናወንን ሰጥቶ በሞገስ የመለሰ እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡