አጋፔሜድ በ2016 ሻሸመኔ ከተማ በመልካ ኦዳ ሆሰፒታል የሰጠው

                አገልግሎት ሪፖርት

blog3

 

" እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ" ኤፌሶን 4፡1

ሻሸመኔ በኢትዮጵያ በምዕራብ አርደሲ ዞን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከአዲስ አበባ 150 ማይልስ ርቃ የምትገኝ ከተማ ስትሆን፤ እ.አ.አ 2012 በነበረው የህዝብ ቆጠራ መሰረት 150,000 ህዝብ ይኖርባታል ተብሎ ይገመታል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን አማርኛ፤ወላይትኛ፤ከምባትኛና ጉራጌኛ ተናጋሪዎችም ይኖሩባታል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሚተዳደረው ከግብርና ጋር በተያያዘ ስራ ቢሆንም የመንግስት ስራና ቱሪዝምም በስፍራው ለብዙዎች አይነተኛ የገቢ ምንጭ ናቸው፡፡

አብዛኛው ህዝብ የእስልም እና የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታይ ሲሆን እንዲሁም የፕሮቴስታንት ና የካቶሊክ ሀይማኖት ተከታዮችም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ሻሸመኔ ከ1948 ጀምሮ ከጀማይካና ከተለያዩ የካረቢያን ሀገሮች መጥተው የሰፈሩ ራስተፈሪያን ያሉባት ከተማ ናት፡፡

የሻሸመኔን ህዝብ ከሚያጠቃው በሽታዎች መካከል 80 ፐርሰንቱ በቀላሉ መከላከያ ሊገኝላቸው የሚችሉ በሽታዎች ናቸው፤ ይሁን እንጂ በቂ ህክምናን ካለማግኘት የተነሳ ብዙዎች በበሽታ ለረጅም ጊዜ ይሰቃያሉ፤ ብሎም ይሞታሉ ፡፡ የአካባቢውን ህዝብ በብዛት ያጠቃሉ ተብለው የሚገመቱ ዋና ዋና የበሽታ አይነቶች እንደሚከተሉት ናቸው፡፡

 • የሳንባ ነቀርሳ እና ኒሞንያ

 • ወባ

 • ታይፎይድ

 • የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን

 • ኤች አይ ቪ/ ኤድስ

 • የአይን በሽታ

 • የስኳር በሽታ

 • ደም ብዛት/ ስትሮክ

 • እንቅርት

 • የጨጓራ በሽታ

 • የወገብ ህመም እና የመሳሰሉት

መልካ ኦዳ ሆስፒታል በሻሽመኔ ከተማ ከሚገኘት ሁለት ሆስፒታሎች መካከል አንዱ ሲሆን የሻሸመኔን ከተማ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውንም ህዝብ ያገለግላል፡፡

በሚኒሶታ በምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን አንድ የአገልግሎት ዘርፍ የሆነው አጋፔሜድ የህክምና ቡድን በኢትዮጵያ ከሚገኘው የክርስቲያን ሜዲካል ዶክተሮችና የጥርስ ሀኪሞች ህብረት ጋር በመተባበር ከ ማርች 13-19 /2016 በመልካ ኦዳ ሆስፒታል በመገኘት በተለያዩ ዘርፎች ለበርካታ ህዝብ የህክምና አገልግሎት አበርክቶ ተመልሷል፡፡ በስራው ላይ ከተሳተፉት በጎ ፈቃደኞች መካከል 18ቱ ከሚኒሶታ የሄዱ ሲሆን 50 የሚሆኑት ዶክተሮች ደግሞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የመጡ ነበሩ፡፡

በወቅቱ በአጠቃላይ 3,372 ሰዎች የተለያየ ህክምና አግኝተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል 1,336 ሰዎች የአይን ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን፤ 700 ለሚሆኑት የአይን በሽተኞች መነፅር ተሰጥቷቸዋል፡፡ የጥርስ ህክምና ከተደረገላቸው172 የሚሆኑ ሰዎች መካከልም 78 ለሚሆኑት የተበላሸ ጥርስ ያላቸው የጥርስ ነቀላ ስራ ተሰርቶላቸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ባሉት ሁለት የኦፐሬሽን ክፍሎችም በርካታ የቀዶ ጥገና ስራ ተሰርቷል፡፡ በመሆኑም 17 ሰዎች ዋና ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል 11 ሰወች በቅድሚያ አስፈላጊው የላቦራቶሪ ስራ ተደርጎላቸው በውጤቱ መሰረት ጎይተር/ እንቅርት ወጥቶላቸዋል፡፡ 35 የሚሆኑ ሰዎችም አነስተኛ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸዋል፡፡ በተለይ በዚህ ቀላላ የቀዶ ጥገና ወቅት በርካታ በሰውነት ላይ የወጡ እጢዎችና የተቋጠሩ ፈሳሾች ከብዙዎች ተወግደዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቀሪዎቹ ከ1,500 በላይ የሚሆኑት ሰዎች የውስጥ ደዌ ህክምና ያገኙ ሲሆን የህፃናት ህክምናም በዚህ ውስጥ ተካቷል፡፡

የዚህ አገልግሎት ሌላው ዋና አላማ ደግሞ ሰዎችን በወንጌል መድረስ እንደመሆኑ መጠን በወቅቱ ለህክምና ለመጡት በርካታ ሰዎች ህክምናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የምስራቹን ወንጌል እነዲሰሙ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም ልባቸውን ለቃሉ የከፈቱ 42 ሰዎች ክርስቶስ ኢየሱስን እንደግል አዳኝ አድርገው በእምነት ተቀብለዋል፡፡

ጌታን እንደግል አዳኝ አድርገው ከተቀበሉት ወገኖች መካከል በተለይ የአንድ ወንድም ምስክርነት ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይህ ሰው በኑሮው ላይ ከደረሰበት ውጣ ውረድ የተነሳ ህይወት ትርጉም ስላጣበት በብስጭት ጋዝ በሰውነቱ ላይ በማፍሰስ ህይወቱን በገዛ እጁ ለማጥፋት ክብሪት ላዩ ላይ ይለኩሳል፡፡ ድርጊቱን ሲፈፅም በአካባቢው ሆነው የተመለከቱ ሰዎች እሳቱን ካጠፉ በኋላ ወደ ሆስፒታል ያመጡታል፡፡ ሆስፒታል እንደደረሰ ተገቢው የድንገተኛ አገልግሎት ተሰጥቶት በማግስቱ የተቃጠለውን የሰውነት ቆዳ ለማንሳት የሚያስችል የቀዶ ጥገና እንደሚደረግለት ተነግሮት ያድራል፡፡

በማግስቱ ለቀዶ ጥገናው ከመግባቱ በፊት በተኛበት ገርኒ ላይ ተራውን በመጠባበቅ ላይ ሳለ፤ ያየችው ነገር ያስደነገጣት አንዲት ነርስ ወደ በሽተኛው ጠጋ ብላ ምን ሆኖ በእሳት ሊቃጠል እንደቻለ ጠየቀችው፡፡ በመሆኑም ከላይ እንደተጠቀሰው የህይወት ተስፋ እንዴት እንደተዳፈነበትና ከመኖር ሞትን እንዴት እንዳስመረጠው ምንም ሳይደብቅ ይነግራታል፡፡ በዚህን ጊዜ በውስጧ ከገባው ርህራሄ የተነሳ እንባና ሲቃ በተሞላባቸው ቃላቶች "ምነው ወንድሜ ለምን ብለህ በስጋም በነፍስም መቃጠልን መረጥክ፡፡ ህይወት እኮ ፈጣሪ ያላት የከበረች ናት፡፡ ክርስቶስ እየሱስ ይወድሀል፡፡ እርሱ ለሰው ልጆች ካለው ታላቅ ፍቅር የተነሳ ነፍሱን ሰለሁላችን ሲል በመስቀል ላይ በመስጠት በኀጢያታችን ምክንያት መሞት ሲገባን፤ ሞታችንን ሞቶ እኛን ከኀጢያት ባርነት ነፃ አድርጎናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው እርሱን በማመን ኀጢያታችንን በመናዘዝ በንስሀ ወደ ፈጠረንና ወደሚወደን ጌታ መመለስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ይህ ጌታ የአንተም ጌታ ነው፡፡ ነፍሱን በመስጠት ፍቅሩን የገለፀልህን፤ የሚወድህን ጌታ እንደግል አዳኝህ አድርገህ በመቀበል የህይወትህ ጌታ ልታደርገው ብትፈልግ ትችላለህ፡፡ እርሱ እውነት፤ህይወትና ብቸኛ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርስ መንገድ ነው፡፡ ህይወትህን በእውነተኛ ደስታ፤ ሰላምና ተስፋ ሊሞላ የሚችል አርሱ ብቻ ነው፡፡ አሁን በዚህች ደቂቃ በልብህ በር ላይ ቆሞ ልብህን ክፈትልኝ እያለ አያንኳኳ ነው፡፡ ልትከፍትለት ፈቃደኛ ነህ? " በማለት ስለክርስቶስ በመመስከር ፈቃደኛነቱን ጠየቀችው፡፡ በጣም በሚደንቅ ሁኔታ ያለምንም ማንገራገር በአይኖቹ ውስጥ በህይወት የመኖርና የተስፋ ጭላንጭል እየታየው አዎን ፈቃደኛ ነኝ በማለት እዛው ባለበት ገርኒ ላይ ሆኖ ጌታን እንደግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ፡፡ ፀሎቱን አድርገው እንደጨረሱ የቀዶ ጥገናውን ከጨረሰ በኋላ ወደ ዋርድ ሲመለስ እርሷም ሆነ ሌሎች ወገኖች መጥተው እንደሚያዩት ተነጋግረው ወደ ኦፐሬሽኑ ክፍል ገባ፡፡

የዚህ ወንድምና የሌሎችም በወቅቱ ጌታን እንደግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉትን አማኞች ስም ዝርዝርና ስልክ ቁጥር ለአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት ተወካይ በማስተላለፍ ቀጣይ የደቀመዝሙር ክትትል እንዲደረግላቸው ተደርጓል፡፡ ክብር ለስሙ ይሁን፡፡

ከዚህም ባሻገር ደግሞ 12 ለሚሆኑ ወላጅና መጠለያ አልባ ለሌላቸው እንዲሁም በኤች አይ ቪ ለተጠቁ ህፃናት ወደፊት ራሳቸውን ለማስቻል እገዛ ሊያደርግ የሚችልና አነስተኛ ስራን ለማቋቋም የሚረዳ መጠነኛ እርዳታ በሀላፊነት ለሚያስፈፅም አካል ተሰጥቷል ፡፡

የአጋፔሜድ የህክምና ቡድን በሻሸመኔ ከተማ በመልካ ኦዳ ሆስፒታል በመገኘት የነፃ ህክምና አገልግሎት ከመስጠቱም በተጨማሪ በሚኒሶታ ከሚገኘው ማተርስ ከተሰኘው በጎ አደራጊ ድርጅት ጋር ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ ያላቸውን የህክምና መሳሪያዎችና መገልገያ እቃዎች በኮንቴነር ሞልቶ በመርከብ በማስጫን ወደስፍራው በመላክ ለህዝብ አገልግሎት ይውል ዘንድ ለሆስፒታሉ አበርክቷል፡፡ በዚህ አጋጣሚ እነዚህን በርካታ መሳሪያዎችና የመገልገያ እቃዎች በነፃ የሰጠንን ማተርስ የተሰኘ ድርጅት በጣም ለማመስገን እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም ኮንቴነሩን በመርከብ ለማስጫን የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን በተደረገው የፈንድ ሬዚንግ ዝግጅትም ሆነ በተለያየ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ ወቅት የተሳተፋችሁትን ሁሉ በአጋፔሜድ እና በሚኒሶታ በምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤ/ክርስቲያን ስም ከልብ የምናመሰግን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

አገልግሎቱ በተጠናቀቀበት ወቅት በመልካ ኦዳ ሆስፒታል የተዘጋጀ የምስጋናና የሽኝት ስነስርአት ተካሄዶ ነበር፡፡

በወቅቱም ፓስተር እንድርያስ ሐዋዝ በሚኒሶታ የምትገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና መጋቢ ስለ አጋፔሜድ አገልግሎ አጀማመርና እንቅስቃሴ ሰፊ ማብራሪያ አድርገዋል፡፡

የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ ተወካይ እንዲሁም የመልካ ኦዳ ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ መሀመድም በበኩላቸው የአጋፔሜድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሆስፒታሉና በሻሸመኔ ህዝብ ላይ ያበረከተውን አስተዋፅኦ በመዳሰስ የምስጋና ንግግር አድርገዋል፡፡ ከንግግራቸውም ማብቂያ ላይ ለቡድኑ ተወካዮች ለአገልግሎቱ ጥቅም ላይ የሚውል ስጦታ አበርክተዋል፡፡

አቶ አብዲ ለገሰ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅም ሆስፒታሉ ከአጋፔሜድ ጋር በመተባበር በአመቱ ውስጥ ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በዝርዝር በማስረዳት ለሆስፒታሉ ስለተደረገው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያላቸውን ከፍተኛ ምስጋና ገልፀዋል፡፡

የአጋፔሜድ አገልግሎት ተወካዮችም ከሁሉ በላይ የአገልግሎቱ ዘርፍ ስራውን ለመስራት ካቀደበት ጊዜ አንስቶ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ አመቱን ሙሉ እርዳታውን ለደቂቃ እንኳን ላላቋረጠው እግዚአብሔር ምስጋና ይግባው በማለት ከልብ አመስግነዋል፡፡ በተለይም የአካባቢውን ሰላም ተቆጣጥሮ አገልግሎቱ ስራውን በሰላም ጀምሮ በሰላምና በድል እንዲጨርስ ማድረጉ ምስጋናቸውን እጥፍ ድርብ አድርጎታል፡፡ ክብሩን እርሱ ብቻ ይውሰድ፡፡

" ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፡፡"መዝሙር 72፡18